፲፬
፩ ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር።
፪ የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና።
፫ እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።
፬ አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው?
፭ ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት።
፮ ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች።
፯ ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም።
፰ የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው።
፱ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።
፲ ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።
፲፩ ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር።
፲፪ ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት።
፲፫ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤
፲፬ ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት።
፲፭ እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤
፲፮ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ።
፲፯ በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።
፲፰ ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ።
፲፱ እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር።
፳ እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው።
፳፩ የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው።
፳፪ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።
፳፫ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።
፳፬ እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው።
፳፭ እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው።
፳፮ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
፳፯ ኢየሱስም። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና።
፳፰ ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።
፳፱ ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው።
፴ ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።
፴፩ እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
፴፪ ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም። ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው።
፴፫ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና።
፴፬ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው።
፴፭ ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና።
፴፮ አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ።
፴፯ መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?
፴፰ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።
፴፱ ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ።
፵ ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም።
፵፩ ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።
፵፪ ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።
፵፫ ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ።
፵፬ አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
፵፭ መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤
፵፮ እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት።
፵፯ በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ።
፵፰ ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን?
፵፱ በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው።
፶ ሁሉም ትተውት ሸሹ።
፶፩ ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥
፶፪ ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።
፶፫ ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ።
፶፬ ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር።
፶፭ የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤
፶፮ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም።
፶፯-፶፱ ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም።
፷ ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው።
፷፩ እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው።
፷፪ ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።
፷፫ ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል?
፷፬ ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።
፷፭ አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።
፷፮ ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥
፷፯ ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።
፷፰ እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ።
፷፱ ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር።
፸ እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት።
፸፩ እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ።
፸፪ ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።