፲፫
፩ እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ አለው።
፪ ኢየሱስም መልሶ። እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው።
፫ በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም።
፬ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት።
፭ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
፮ ብዙዎች። እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ።
፯ ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው።
፰ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
፱ እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።
፲ አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።
፲፩ ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።
፲፪ ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤
፲፫ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
፲፬ ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥
፲፭ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥
፲፮ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።
፲፯ በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።
፲፰ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤
፲፱ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና።
፳ ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።
፳፩ በዚያን ጊዜም ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም። እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤
፳፪ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ።
፳፫ እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ።
፳፬ በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥
፳፭ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።
፳፮ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።
፳፯ በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።
፳፰ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤
፳፱ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ።
፴ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።
፴፩ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።
፴፪ ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም።
፴፫ ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።
፴፬ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ።
፴፭ እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና
፴፮ ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ።
፴፯ ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።