፬
፩-፫ እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።
፬ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤
፭ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
፮ ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ።
፯ ነገር ግን ለዚህ ዓለም ከሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ። እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ።
፰ ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።
፱ ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤
፲ ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።
፲፩-፲፫ እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ።
፲፬ በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፥ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል።
፲፭ ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር።
፲፮ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።