፲፫
፩ አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ።
፪ ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።
፫ ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥
፬ ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት።
፭ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው።
፮ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ።
፯ ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።
፰ ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።
፱ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።
፲ ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።
፲፩ ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር።
፲፪ በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል።
፲፫ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል።
፲፬ በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል።
፲፭ የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው።
፲፮ ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥
፲፯ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ።
፲፰ አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።