፳
፩ አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና።
፪ እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት።
፫ መልሶም። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤
፬ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው።
፭ እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤
፮ ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ።
፯ መልሰውም። ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት።
፰ ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።
፱ ይህንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይላቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ አገር ሄደ።
፲ በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት።
፲፩ ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት።
፲፪ ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት።
፲፫ የወይኑም አትክልት ጌታ። ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ።
፲፬ ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ።
፲፭ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል?
፲፮ ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ።
፲፯ እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ። እንግዲህ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው?
፲፰ በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል አለ።
፲፱ የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።
፳ ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት።
፳፩ ጠይቀውም። መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤
፳፪ ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት።
፳፫ እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ። ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤
፳፬ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም። የቄሣር ነው አሉት።
፳፭ እርሱም። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።
፳፮ በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።
፳፯ ትንሣኤ ሙታንንም የሚክዱ ከሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ቀርበው ጠየቁት፥
፳፰ እንዲህ ሲሉ። መምህር ሆይ፥ ሙሴ። ሚስት ያለችው የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን።
፳፱ እንግዲያስ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የፊተኛውም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤
፴-፴፪ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች።
፴፫ እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች?
፴፬ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥
፴፭ ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥
፴፮ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።
፴፯ ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤
፴፰ ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
፴፱ ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው። መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት።
፵ ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም።
፵፩ እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?
፵፪-፵፬ እንግዲህ ዳዊት። ጌታ ብሎ ይጠራዋል፥ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?
፵፭ ሕዝቡም ሁሉ ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን።
፵፮ ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤
፵፯ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።