፮
፩ ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።
፪ ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።
፫ አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።
፬ ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤
፭ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።
፮ ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል።
፯ አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤
፰ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።
፱ ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።
፲ እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።
፲፩ እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ።
፲፪ በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው።
፲፫ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም።
፲፬ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።
፲፭ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።
፲፮ በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።
፲፯ እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ።
፲፰ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።