፭
፩ ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።
፪ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥
፫ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።
፬ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን።
፭ ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።
፮-፰ ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል።
፱ ስለዚህ ደግሞ ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን እርሱን ደስ የምናሰኝ ልንሆን እንቀናለን።
፲ መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።
፲፩ እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ።
፲፪ በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም።
፲፫ እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው።
፲፬ ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤
፲፭ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።
፲፮ ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።
፲፯ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።
፲፰ ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤
፲፱ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።
፳ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።
፳፩ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።